Web Content Display
የጽ/ቤቱ ሥልጣንና ተግባር
1.የርእሰ-መስተዳድሩ ጽህፈት ቤት በሕገ-መንግሥቱ፣ በአዋጁና በዚህ ደንብ መሠረት የክልሉ መራሄ-መንግሥት ዋና የዕለት-ተለት ሥራዎች ማከናወኛና የምክር ቤቱ ሥብሰባዎች ማስተናገጃ ማዕከል ነው፡፡
2.በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ሥር የሰፈረው አጠቃላይ ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ ጽህፈት ቤቱ በዚህ ደንብ መሠረት የሚከተሉት ዝርዝር ስልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡-
ሀ) ለርዕሰ-መስተዳድሩ፣ለምክትል ርዕሰ-መስተዳድሩ፣ ለዋና የሕግ አማካሪውና የበላይ አመራሩን በሙያቸው እንዲያግዙ ለተመደቡ ሌሎች ተሿሚዎች ከሥራ ሃላፊነታቸው ጋር በተያያዘ ሁለገብ አገልግሎት ይሰጣል፣ ለዚህም የሚያስፈልገው ብቁ የሰው ኃይልና ቁሳዊ ግብአት ተሟልቶና ተደራጅቶ መገኘቱን ያረጋግጣል፤
ለ) ዝርዝሩ ይህንን ደንብ ለማስፈፀም በሚወጣ መመሪያ የሚወሰን ሆኖ ለርዕሰ-መስተዳድሩ፣ ለምክትል ርዕሰ-መስተዳድሩ፣ ለምክር ቤቱ አባላትና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሌሎች የክልሉ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገቢውን የፕሮቶኮል ሽፋን ይሰጣል፤
ሐ) በአዋጁና በሌሎች ሕጎችመሠረት ለርዕሰ-መስተዳድሩ ተጠሪ የሆኑ አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶችንና ተቋማትን ለይቶ ይመዘግባል፣ ከርዕሰ- መስተዳድሩ ጋር የሚኖራቸውን የሥራ ግንኙነት በማቀላጠፍ ረገድ ያግዛል፡፡
የካቢኔ ጉዳዮችን በተመለከተ፡
ሀ) ለምክር ቤቱ አባላት መደበኛና አስቸኳይ ስብሰባዎች የሚያስፈልጉትን የመሰብሰቢያ ቦታዎች ያሰናዳል፣ የሥራ ማቀላጠፊያ መሳሪያዎችንና ሌሎች ተዛማጅ ግብአቶችን በወቅቱ ያቀርባል፣ ለተሰብሳቢዎች ተገቢው መስተንግዶ ተሟልቶ መቅረቡን ያረጋግጣል፤
ለ) የምክር ቤቱ ስብሰባ ቃለ-ጉባኤዎች በአግባቡ ተይዘው፣ በወቅቱ ተፈርመው፣ ትክክለኛነታቸው ተረጋግጦና በአይነት እየተለዩ ቁጥር ከተሰጣቸው በኋላ ተመዝግበው የሚቀመጡበትን የሥራ ክፍል ያሰናዳል፣ ያደራጃል፣ አስተማማኝ ጥበቃ ማግኘታቸውን ያረጋግጣል፣ ለዚህም የሰለጠነ የሰው ኃይል መመደቡን ያረጋግጣል፤
ሐ) ምክር ቤቱ በመደበኛም ሆነ በአስቸኳይ ስብሰባዎቹ ተወያይቶ የደረሰባቸውን ድምዳሜዎችና ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች የመፈጸም ወይም የማስፈጸም ሀላፊነት ለተሰጣቸው አካላት በኦፊሴል ያስተላልፋል፤
መ) ምክር ቤቱ ተወያይቶ ያጸደቃቸው ደንቦች በወቅቱ ወደእንግሊዝኛ ቋንቋ ተተርጉመው በክልሉ ዝክረ-ሕግ ጋዜጣ ይታተሙና ለህዝብ ይሰራጩ ዘንድ ወደክልሉ ሕግ አውጪ ምክር ቤት እንዲላኩ ያደርጋል፡፡
የህዝብ ቅሬታና አስተዳደራዊ ፍትህን በተመለከተ፡-
ሀ) አስተዳደራዊፍትህ ፈልገው ወደ ጽህፈት ቤቱ የሚመጡትን ባለጉዳዮች ተቀብሎ ያስተናግዳል፣ ጉዳያቸውን በማጣራት ወቅታዊና አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣል፣ ወይም በክፍሉ ደረጃ ሊፈታ የማይችል ሆኖ ሲያገኘው ተገቢው ምላሽ ይሰጥበት ዘንድ አስተያየቱን በጽሁፍ አደራጅቶ ቅሬታው ለቀረበበት አካል ወይም አግባብ ላለው የክልሉ መንግሥት መስሪያ ቤት የበላይ ኃላፊ ያስተላልፋል፤
ለ) የክልሉ መንግሥት ተቋማት ከሚሰጧቸው አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ከዜጎች የሚቀርቡ ቅሬታዎችንና አቤቱታዎችን ተቀብሎ በሚመረምርበትና በሚያጣራበት ጊዜ ለሥራው አስፈላጊ የሆኑትን ኦፊሴላዊ ሰነዶችና ሌሎች ማስረጃዎች አስቀርቦ ይመለከታል፣ ያጠናል፤
ሐ) ደረጃውን የጠበቀና ሁሉንም ያለአድልዎ ለማስተናገድ የሚያስችል የህዝብ ቅሬታዎች አቀራረብና አቀባበል ስርዓት ቀርጾ በስራ ላይ እንዲውል ያደርጋል፣ ይህንኑ በተለያዩ አመቺ ዘዴዎች ለተጠቃሚው ህብረተ-ሰብ ያስተዋውቃል፤
መ) ከህዝብ የሚቀርቡ የአስተዳደራዊ ፍትህ መጠየቂያ አቤቱታዎችን ዓይነት፣ ብዛትና መንስኤ በየጊዜው እያጠና የሕዝብ አቤቱታዎች በየደረጃው ባሉ የክልሉ መንግሥት አስተዳደር አካላት መፍትሄ የሚያገኙበትን መንገድ በመጠቆም ለውሳኔ ሰጪ አካላት ያቀርባል፡፡
የፕሬስና የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን በተመለከተ፡-
ሀ) ምክር ቤቱ የሚያወጣቸውን ጋዜጦች፣ መጽሄቶችና በራሪ ጽሁፎች ዝግጅት፣ ህትመትና ሥርጭት ሥራ በበላይነት ይመራል፣ ይከታተላል፤
ለ)የምክር ቤቱ ህትመትና ኦዲዮቪዥዋል መረጃ አገልግሎት በሰለጠነ የሰው ሀይልና በዘመናዊ ዘዴ እንዲደራጅና እንዲጠናከር ያደርጋል፤
ሐ) ለምክር ቤቱ አባላት፣ ለቋሚ ኮሚቴዎች፣ ለርእሰ-መስተዳድሩ አማካሪዎችና ሌሎች ደጋፊ ኤክስፐርቶች የቤተ- መጻህፍት፣ የምርምርና የመረጃ አገልግሎት እንዲቀርብ ያደርጋል፤
መ) ዝርዝሩይህንን ደንብ ለማስፈፀም በሚወጣ መመሪያ የሚወሰን ሆኖ ከሃገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ለሚመጡ የክልሉ እንግዶች በምክር ቤቱ ስም ሁለገብ የመስተንግዶ አገልግሎት ይሰጣል፤
ሠ) በምክር ቤቱ ስም የሚጠሩ ክልል-አቀፍ አውደ-ጥናቶች፣ ሲምፖዚየሞች፣ ኮንፍረንሶችና ሌሎች ስብሰባዎች አስቀድሞ በተቀረፀላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲከናወኑ ያደርጋል፡፡
3.የጽኅፈት ቤቱ መደበኛ እቅዶችና ክልላዊ ባህርይ ያላቸው መርሃ-ግብሮች እርስበርስ ተጣጥመው የሚፈጸሙበትን የተቀናጀ የአሠራር ስልት ይቀይሳል፣ ገቢራዊ ያደርጋል፤
4.በመደበኛና በካፒታል በጀት ለሚያከናውናቸው የሥራ ፕሮግራሞች የሚያስፈልገውን አመታዊ የማስፈፀሚያ በጀት ረቂቅ ያዘጋጃል፣ ስልጣን ላለው አካል ቀርቦ ሲፀድቅለትም በሥራ ላይ እንዲውል ያደርጋል፤
5.በሥሩ የተዋቀሩ አደረጃጀቶች ለህዝቡ ቀልጣፋና ደረጃውን የጠበቀ መንግሥታዊ አገልግሎት መስጠታቸውን ይከታተላል፣ ጉድለት መፈፀሙን ሲረዳም አፋጣኝ የእርምትና የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል፤
6.በክልሉ ውስጥ የሚገኙትን የበታች አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች እንዳስፈላጊነቱ በሰው ሃይል አቅም ግንባታና በአገልግሎት ማቀላጠፊያ መሣሪያዎች አቅርቦት ረገድ ይደግፋል፣ ያጠናክራል፣ ብቃት ባለውና ሥነ-ምግባሩን በጠበቀ የሰው ኃይል መገልገላቸውን ይከታተላል፤
7.ለተዋረድ የአስተዳደር ጽህፈት ቤቶች በየጊዜው የሚመደበው የአይነትም ሆነ የጥሬ ገንዘብ ሃብት ውጤታማ በሆነ መንገድ በሥራ ላይ የዋለ ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ አስተማማኝ የቁጥጥር ሥርዓት ይዘረጋል፣ ለዚህም ስኬታማነት የውስጥ ኦዲት አገልግሎት እንዲጠናከር ያደርጋል፤
8.በየደረጃው በሚገኙት የአስተዳደር ጽህፈት ቤቶች ዘንድ እቅድ የማውጣት፣ ይህንኑ ተግባራዊ የማድረግና አፈፃፀሙን የመገምገም ባህል በሠራተኛው ተሳትፎ እንዲጎለብት ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል፤
9.በሕግ መሰረት ውሎችን ይዋዋላል፣ የንብረት ባለቤት ይሆናል፣ በሥሙ ይከሣል፣ ይከሰሳል፤
10.አላማዎቹን ከግብ ለማድረስ በርዕሰ-መስተዳድሩ የሚሰጡትን ሌሎች ተዛማጅ ተግባራት ያከናውናል፡፡
የጽ/ቤቱ አመራርና ተጠሪነት
1.ጽህፈት ቤቱ የሚመራው የብሔራዊ ክልላዊ መንግሥቱ ርዕሰ-መስተዳድር ለዚሁ ዓላማ በሚሾማቸው ዋናና ምክትል ሀላፊዎች ይሆናል፡፡
2.የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ተጠሪነቱ ለርዕሰ-መስተዳድሩ ነው፡፡
3.የምክትል ሀላፊው ተጠሪነት ለጽህፈት ቤቱ የበላይ ሀላፊ ይሆናል፡፡
የጽ/ቤቱ ኃላፊ ሥልጣንና ተግባር
1.የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ከዚህ በላይ በአንቀጽ 9 ሥር የተመለከቱትን የጽህፈት ቤቱን ሥልጣንና ተግባራት በሥራ ላይ ያውላል፡፡
2.በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (1) ስር የሰፈረው አጠቃላይ ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ፡-
ሀ)ከርዕሰ-መስተዳድሩ በሚሰጠው አመራር መሠረት የጽሕፈት ቤቱን ሥራዎች በበላይነት ይመራል፣ ጽህፈት ቤቱን ያስተዳድራል፤
ለ)የጽህፈት ቤቱን ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች በክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መሠረት ይቀጥራል፣ ያስተዳድራል፣ ያሰናብታል፤
ሐ)የጽህፈት ቤቱን ዓመታዊ የሥራ ዕቅድ፣ የማስፈፀሚያ በጀትና የድርጊት መርሃ-ግብር አዘጋጅቶ ለርዕሰ-መስተዳድሩ ያቀርባል፣ ሲፈቀድለትም በተግባር ላይ እንዲውል ያደርጋል፤
መ) በጽህፈት ቤቱ ስም የባንክ ሂሳብ ይከፍታል፣ ያንቀሳቅሳል፤
ሠ) ለጽህፈት ቤቱ በተፈቀደው በጀትና የሥራ ፕሮግራም መሠረት ገንዘብ ወጪ ያደርጋል፤
ረ) ከሶስተኛ ወገኖች ጋር በሚደረጉ ግንኙነቶች ጽህፈት ቤቱን ይወክላል፤
ሰ) የጽህፈት ቤቱን የሥራ እንቅስቃሴና የሂሣብ ሪፖርት አዘጋጅቶ ለርዕሰ-መስተዳድሩና ለክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ያቀርባል፤
ሸ) ከተልእኮው ጋር በተያያዘ ከርዕሰ-መስተዳድሩ በኩል የሚመሩለትን ሌሎች ተዛማጅ ተግባራት ያከናውናል፡፡
የምክትልኃላፊው ስልጣንና ተግባር
የጽህፈት ቤቱ ምክትል ሀላፊ ተጠሪነቱ ለጽህፈት ቤቱ የበላይ ሀላፊ ሆኖ፡-
1.በጽህፈት ቤቱ ሀላፊ ተለይተው የሚሠጡትን ተግባራት ያከናውናል፤
2.የጽህፈት ቤቱ የበላይ ኃላፊ በማይኖርበት ወይም ስራውን ለማከናወን በማይችልበት ጊዜና ሁኔታ እርሱን ተክቶ ይሠራል፡፡
ስለርዕሰ-መስተዳድሩ የሕግ አማካሪና ሌሎች አማካሪዎች
1.ርዕሰ-መስተዳድሩ በክልሉ ጠቅላይ አቃቤ-ሕግ ማአረግ የሚሾም ዋና የሕግ አማካሪ ይኖረዋል፡፡
2.ርዕሰ-መስተዳድሩ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 60ና በአዋጁ አንቀጽ 8 ንኡስ አንቀጽ (2) ድንጋጌዎች ስር የተጣለበትን ፈርጀ-ብዙ ሀላፊነት ለመወጣት አስፈላጊ ሆኖ ባገኘው መጠን በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊ፣ በህዝብ ደህንነት፣ በበይነ-መንግሥታዊ ግንኙነቶች አመራር፣ በመሰረተ-ልማትና በመሳሰሉት ጉዳዮች የኤክስፐርቲስ ድጋፍ የሚያደርጉለትና ከየሙያ መስኩ የተወጣጡ ሌሎች አማካሪዎች ይኖሩታል፡፡
3.ርእሰ-መስተዳድሩ ከዚህ በላይ በንኡስ አንቀጽ (2) ስር በተጠቀሱት የስራ ዘርፎች አማካሪዎችንም ሆነ ኤክስፐርቶችን እንደተገቢነቱ በቋሚነት ሰይሞ ወይም በጊዜያዊነት መድቦ ሊያሰራ ይችላል፡፡
4.የነዚህ አማካሪዎች ዝርዝር ተግባርና ሀላፊነት ርእሰ-መስተዳድሩ በሚያወጣው መመሪያ ይወሰናል፡፡
5.የተሿሚ አማካሪዎች ተጠሪነት ለርእሰ-መስተዳድሩ ይሆናል፡፡