Web Content Display Web Content Display

ደንብ ቁጥር 179/2011 ዓ.ም

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ-መስተዳድር ጽህፈት ቤት እንደገና ማቋቋሚያና ሥልጣንና ተግባራት መወሰኛ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ደንብ

ደንብ ቁጥር 179/2011 ዓ.ም

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ-መስተዳድር ጽህፈት ቤትን እንደገና ለማቋቋምና ሥልጣንና ተግባራቱን ለመወሰን የወጣ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ደንብ

የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ጽህፈት ቤት በተሻሻለው የብሄራዊ ክልሉ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 62 ንዑስ አንቀጽ (1) ድንጋጌ ሥር በተመለከተው አኳኋን የክልላዊ መንግሥቱ ዋና አስፈፃሚና መራሄ-መንግሥት ሥራዎች ማከናወኛ መሥሪያ ቤት ሆኖ እውቅና ያገኘና ዝርዝር ስልጣንና ሀላፊነቱም ራሱን በቻለ ሕግ እንደሚደነገግ አስቀድሞ የተገለጸ በመሆኑ፤ በቅርቡ የተካሄደውን የአስፈጻሚ አካላት አደረጃጀት ክለሳና የሀላፊነት ሽግሽግ ተከትሎ ይኸው ጽህፈት ቤት የተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 185/2003 ዓ.ም ተሽሮ በደንብ እንዲተካ የተወሰነ በመሆኑ፤

ተቋሙ ሕገ-መንግሥቱን መነሻ በማድረግ ለርእሰ-መስተዳድሩ ከተሠጠው ፈርጀ-ብዙ ኃላፊነት የተነሣ ከዕለት-ተለት ሥራ ማከናወኛ ጽህፈት ቤትነት አልፎ የክልል መስተዳድር ምክር ቤቱ አበይት የመወያያ አጀንዳዎች የሚስተናገዱበት፣ የሚጣሩበትና የውሣኔ ሠነዶች ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ የሚሠናዱበት ብሎም ለተጠቃሚዎች የሚሠራጩበት ሆኖ  መገኘት ያለበት በመሆኑ፤

ይልቁንም በሁለገብ ልማት፣ መፋጠን በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታና በመልካም አስተዳደር ዘርፎች አተኩረው እንዲሠሩ በክልሉ ውስጥ የተቋቋሙት የተለያዩ አስፈፃሚ አካላት በሕግ የተሠጣቸውን ተልዕኮ ለማሣካት በተናጠል የሚያካሂዱት ጥረት በክልል ደረጃ ይበልጥ ተቀናጅቶ የሚመራበትና አፈፃፀማቸው በየጊዜው እየተገመገመ ከሥትራቴጃዊ ግቦች አኳያ  የሚቃኝበት ተቋም ሆኖ መውጣት እንዳለበት በመታመኑ፤

ጽህፈት ቤቱ የበላይ አመራሩን በተሻለ አቅም ለማገልገል በሚያስችለው ሁኔታ ተደራጅቶ ብቃት ያለውና የተሳለጠ አገልግሎት ይሠጥ ዘንድ እስካሁን ሲሠራበት የነበረውን ቁመና የማስተካከል ፋይዳ ያለው የተሟላና ለተለዋዋጭ ሁኔታዎች ምላሽ የሚሰጥ የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልገው በመታመኑ፤

 

ከሁሉም በላይ ክልሉ ከፌድራሉ መንግሥት አካላትና  ከሌሎች አቻ ክልሎች ጋር ባሉት በይነ-መንግሥታዊ ግንኙነቶችና ሥትራቴጃዊ የትኩረት መስኮች ረገድ ጽህፈት ቤቱን የላቀ ድጋፍ የመስጠት አቅም ባለው በቂ የሰው ሀይልና የቴክኖሎጂ ግብዓት ተጠቃሚ በሆነ አደረጃጀት ማጠናከርና ለዚህም የሚያስፈልገው የአይነት ሀብትም ሆነ የፋይናንስ መሠናዶ እንዲመቻችለት የሚያደርግ ሥርዓት መዘርጋት ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ፤

የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በተሻሻለው የክልሉ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 58 ንዑስ አንቀጽ (7)ና. የብሄራዊ ክልላዊ መንግሥቱን አስፈጻሚ አካላት እንደገና ለማቋቋምና ስልጣንና ተግባራቸውን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 264/2011 ዓ.ም አንቀጽ ፸፸7 ንኡስ አንቀጽ፺(2) ድንጋጌዎች ሥር በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህንን ደንብ አውጥቷል፡፡

 

ክፍል አንድ

ጠቅላላ ድንጋጌዎች

1.  አጭር ርዕስ

ይህ ደንብ የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ጽህፈት ቤት እንደገና ማቋቋሚያና ሥልጣንና ተግባራት መወሰኛ ክልል መስተዳድረር ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 179/2011 ዓ.ም” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

2.  ትርጓሜ

የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ ደንብ ውስጥ፡-

1.  "አዋጅ ማለት ተሻሽሎ የወጣው የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት አስፈጻሚ አካላትን እንደገና ለማቋቋምና ስልጣንና ተግባራቸውን ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 264/2011 ዓ.ም ነው፡፡

2.  ሕገ-መንግሥት" ማለት በ1994 ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣው የአማራ ክልል ሕገ-መንግሥት ሲሆን ዘግይተው የተደረጉ ወይም ወደፊት የሚደረጉ ማሻሻያዎችን ይጨምራል፡፡

3.  “ርዕሰ-መስተዳድር” ማለት በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 60 ንዑስ አንቀጽ (1) ድንጋጌ ሥር የተመለከተው አካል ነው፡፡

4.  “ምክር ቤት” ማለት በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 60ንዑስ አንቀጽ (1) ድንጋጌ ስር የተመለከተው አካል ነው፡፡

3.  የተፈፃሚነት ወሰን

ይህ ደንብ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 62 ንዑስ አንቀጽ (1) ድንጋጌ ስር በተመለከተው የክልሉ ርዕሰ-መሥተዳድር ጽህፈት ቤትና እንደተገቢነቱ በብሔረ-ሰብ አስተዳደር፣ በዞን፣ በዎረዳ፣ በከተማና በቀበሌ አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች ላይ ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡

ክፍል ሁለት

ስለርዕሰ-መስተዳድሩ  ጽህፈት ቤት እንደገና መቋቋም፣ ዓላማ፣ ሥልጣንና አደረጃጀት

4.  ስለመቋቋምና ተጠሪነት

1.  የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ጽህፈት ቤት /ከዚህ በኋላ/ “ጽህፈት ቤቱ” እየተባለ የሚጠራው አካል ራሱን የቻለና ሕጋዊ ሰውነት ያለው የክልሉ መንግሥታዊ መስሪያ ቤት ሆኖ በዚህ ደንብ ተቋቁሟል፡፡

2.  የጽህፈት ቤቱ ተጠሪነት ለርዕሰ-መስተዳድሩ ይሆናል፡፡

3.  የርዕሰ-መስተዳድሩ ጽህፈት ቤት በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 62 ንዑስ አንቀጽ (2)ና በአዋጁ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ (1) ሥር በተደነገገው መሠረት የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ጭምር ሆኖ እንዲያገለግል የተዋቀረ ነው፡፡

4.  በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (3) መሠረት ለጽህፈት ቤቱ የተሰጠው ተጨማሪ ተልዕኮ በብሔረ-ሰብ አስተዳደሮች ወይም በዞን፣ በወረዳ፣ በከተማና በቀበሌ አስተዳደሮች ለተቋቋሙት ወይም ወደፊት ለሚቋቋሙ ጽህፈት ቤቶች ጭምር በተመሣሣይ የሚሠራ ይሆናል፡፡

5.  ዓላማዎች

ጽህፈት ቤቱ በዚህ ደንብ መሠረት የሚከተሉት ዓላማዎች ይኖሩታል፡-

1.  ለርዕሰ-መስተዳድሩም ሆነ እርሱ ለሚመራው ከፍተኛ አስተዳደራዊና አስፈፃሚ አካል ደረጃውን የጠበቀና ሕገ-መንግሥታዊ ሀላፊነቱን በብቃት ለመወጣት የሚያስችለውን ሁለገብ ድጋፍ መሥጠትና ይህንኑ ግልፅነት ባለውና ውጤታማነቱ በተረጋገጠ መንገድ ማከናወንና፤

2.  የበላይ አመራሩ ከሚያስተባብራቸው ክልል-አቀፍ አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶችና በተዋረድ ከሚቆጣጠራቸው የየርከኑ አስተዳደር አካላት ጋር ያሉት ግንኙነቶች እንዲሣለጡና በሕግ የበላይነት ላይ ተመስርተው እንዲተገበሩ በማድረግ በበላይና በበታች የመንግሥት አካላት መካከል ግልፅ የሆነና ተጠያቂነት ያለበት የአሠራር ሥርዓት ማስፈን፡፡

6.  መደበኛአድራሻ

 የጽህፈት ቤቱ መደበኛ አድራሻ በክልላዊ መንግሥቱ መቀመጫ፣ በባህርዳር ከተማ ነው፡፡

7.  ስለተዋረድ የአስተዳደር ጽህፈት ቤቶች እውቅናና አደረጃጀት

በክልሉ ውስጥ የታቀፉት የብሔረ-ሰብ አስተዳደሮች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎች፣ ከተሞችና ቀበሌዎች በየተቋቋሙበት እርከን የራሳቸው የሆነና ከርዕሰ-መስተዳድሩ ጽህፈት ቤት ጋር ተቀራራቢ ተልዕኮ የተሰጣቸው የተዋረድ አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች የሚኖሯቸው ሲሆን እነዚሁ ጽህፈት ቤቶች በዚህ ደንብ መሠረት ሕጋዊ ሰውነት አግኝተው እንደገና  ይደራጃሉ፡፡

8.  ድርጅታዊ አቋም

1.  ጽህፈት ቤቱ በዚህ ደንብ መሠረት የሚከተሉት አካላት ይኖሩታል፡-

ሀ. በቢሮ ሀላፊና ምክትል ሀላፊ መአረግ በርእሰ-መስተዳድሩየሚሾሙ ዋናና ምክትል ሀላፊዎች፤

ለ. የካቢኔ ጉዳዮች ሴክሬታሪያት፤

ሐ. የህዝብ ቅሬታና የአስተዳደራዊ ፍትህ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት፤

መ. የፕሬስና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት፤

ሠ. በሂደትና በንዑስ ሂደት የሚደራጁ ሌሎች ዋናና ደጋፊ የሥራ ክፍሎች፡፡

2.  ከዚህ በላይ በንኡስ አንቀጽ (1) ከፊደል ተራ ቁጥር ለ. እስከመ. ድረስ የተጠቀሱትን ዳይሬክቶሬቶች የሚመሩት ሰዎች በምክትል ቢሮ ሀላፊ መአረግ በርእሰ-መስተዳድሩ የሚሾሙ ሲሆን ተጠሪነታቸው ለጽህፈት ቤቱ የበላይ ሀላፊ ይሆናል፡፡