News

Guest የአማራ ክልል የኮሮና ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ኮማንድ ፖስት በክልሉ አራት ከተሞች ምንም ዓይት የሕዝብና የሕዝብ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዳይኖር ውሳኔ አስተላለፈ። ባሕር ዳር፡ መጋቢት 22/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል የኮሮና ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ኮማንድ ፖስት ከነገ መጋቢት 23/2012ዓ.ም ከቀኑ 6፡00 ጀምሮ በባሕር ዳር፣ እንጅባራ፣ ቲሊሊና አዲስ ቅዳም ከተሞች ማንኛውም ዓይነት የተሽከርካሪም ሆነ የሕዝብ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ውሳኔ አስተላልፏል። የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ጌትነት ይርሳው እንደተናገሩት በሕዝብና በሕዝብ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ለተከታታይ 14 ቀናት የሚቆይ ገደብ ተጥሏል። ኮማንድ ፖስቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው ወረርሽኙ ሊያስከትለው የሚችለውን ተጨማሪ ቀውስ ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነም ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል። እገዳው በልዩ ሁኔታ የሚንቀሳቀሱ የደረቅና የፈሳሽ ጭነት ተችከርካሪዎችን አይጨምርም። የድንገተኛ አገልግሎት የሚሰጡና የወረርሽኙ በጎ ፍቃደኞች ግን መንቀሳቀስ ይችላሉ። በአራቱ ከተሞች ወረርሽኙን ለመከላከል ግብዓት የሚሆኑ ምግብና የንጽሕና መጠበቂያ አቅራቢዎች ከኮማንድ ፖስቱ ልዩ ፈቃድ ተስጥቷቸው እንዲቀሳቀሱ እንደሚደረግም መግለጫው አመላክቷል፡፡ የውኃና ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሠራተኞች ግን እንዲንቀሳቀሱ ይደረጋል። እገዳው በተጣለባቸው ከተሞች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ውሳኔው ተፈፃሚ እንዲሆን የተለመደ ትብብራቸውን መወጣት እንዳለባቸውና አቅማችሁ የፈቀደውን ድጋፍ በመለገስ አጋርነታቸውን እንዲያሳዩም ጥሪ ቀርቧ። የወረርሽኑ አሳሳቢነት እየታየም በሌሎች ከተሞች ተመሳሳይ ርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚችሉ አቶ ጌትነት አስረድተዋል። በዚህ ሂደት የተላለፉ መመሪዎችን የማይፈፅሙ ሰዎችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የሚመለካታቸው የፀጥታ አካላት ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስ እንዳባቸው ተጠርጥረው የነበሩ 27 ግለሰቦች ክትትል ሲደረግላቸው ነበር፤ በተደረገላቸው የላቦራቶሪ ምርመራ 25 ነፃ ሲሆኑ ሁለቱ ቫይረሱ እንዳለባቸው መረጋጡ ትናንት ይፋ መደረጉ ይታወቃል።