የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት የክልሉ ከፍተኛ የፖለቲካ ስልጣን ባለቤትና የክልሉ ህዝብ ሉዓላዊነት መገለጫ በመሆን በህገ መንግስቱ የተጣለበትን ዘርፈ-ብዙ ኃላፊነት እየተወጣ ይገኛል፡፡ በክልሉ የሚካሄደውን ሁለንተናዊ የልማትና የዕድገት እንቅስቃሴ እየመራና እየደገፈ በክልሉ ለሚታየው አወንታዊ ለውጥ የአመራር ሚናውን ተጫውቷል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት ወረዳና ከተማ አስተዳደርን መሰረት በማድረግ የተመረጡ 294 የምክር ቤት አባላት አሉት፡፡ የምክር ቤቱ አባላት ነፃ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነና ድምፅ በሚስጢር በሚሠጥበት ስርዓት በየአምስት ዓመቱ በህዝብ የሚመረጡ ናቸው፡፡ የምክር ቤቱ አባላት የመላው የክልሉ ህዝብ ተወካዮች ሲሆኑ በህገ መንግስቱ እንደተደነገገው ተጠሪነታቸውም ለህገ-መንግስቱ፣ ለመረጣቸው ህዝብ እና ለራሳቸው ህሊና ብቻ ነው፡፡

 

የክልሉ ምክር ቤት በክልሉ ህገ-መንግስት አንቀጽ 49 በውል ተለይቶ የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር  መሰረት በማድረግ ተግባራትን ያከናውናል፡፡ በዚህ መሰረት ምክር ቤቱ፡-

 • የክልሉ የህግ አውጭ አካል ነው፤
 • የፌዴራሉን ህገ-መንግስትና ሌሎች ህጐችን የማይፃረሩ ህጐችን ያወጣል፤
 • በክልሉ ውስጥ የአስተዳደር እርከኖችን ወይም የራስን በራስ አስተዳደራዊ አካባቢዎችን ያቋቁማል፤
 • ከአጐራባች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት ጋር የሚደረጉ ስምምነቶችን ያፀድቃል፤
 • ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ርዕሰ መስተዳድሩን በምርጫ ይሰይማል፣ በርዕሰ መስተዳደሩ አቅራቢነት የክልሉን መስተዳድር ምክር ቤት አባላት    ሹመት ያፀድቃል፤
 • በርዕሠ መስተዳደሩ አቅራቢነት የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዝዳንት፣ ምክትል ኘሬዝዳንት፣ ዋና ኦዲተርና ምክትል ዋና ኦዲተሩን ይሾማል፤
 • በህጉ መሰረት ምህረት ያደርጋል፣ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ለመጠበቅ የሚያስፈልጉ መመሪያዎችን ያወጣል፣ የፀጥታና የፖሊስ ኃይሎችን ያቋቁማል፤
 • የብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድሩን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ኘሮግራሞች ያፀድቃል፤
 • የብሔራዊ ክልሉን የገቢ ምንጮች የሚመለከቱ ህጐችን ያወጣል፣ የራሱን በጀት መርምሮ ያፀድቃል፤
 • ለማህበራዊ አገልግሎቶች መስፋፋት፣ ለኢኮኖሚያዊ ልማት መፋጠን ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አስፈላጊ የሆኑ ተቋማትን ያቋቁማል፤
 • ለክልል መንግስት በተከለለው የገቢ ምንጭ በክልሉ ውስጥ ግብርና ታክስ ይጥላል፤
 • የክልል መስተዳደሩን የሰራተኛ አስተዳደርና የስራ ሁኔታዎችን በተመለከተ ህግ ያወጣል፤
 • ለክልሉ መንግስት በተሰጠው ስልጣን መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጣል፤
 • የአገሪቱንና የክልሉን ህግጋት - መንግስታት፣ አዋጆችና ሌሎች ህጐችን በክልሉ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝርዝር የማስፈፀሚያ ደንቦችን ያወጣል፤
 • የክልሉን ርዕሰ መስተዳድርና ሌሎች የክልሉን መንግስት ባለስልጣናት ለጥያቄ ይጠራል፣ የአስፈፃሚውን አካል አሰራር ይከታተላል፣ ይመረምራል፡፡