Web Content Display Web Content Display

Return to Full Page

ለጋዜጠኞች ስልጠና ተሰጠ

  የአማራ ገቢዎች ባለስልጣን በገቢ ግብር አዋጅ ደንቦችና መመሪያዎች አፈጻጸም ዙሪያ ለአማራ ብዙሀን መገናኛ ድርጅት ጋዜጠኞች ከግንቦት 2 እስከ 3 2006 ዓ/ም ለሁለት ቀናት በዳንግላ ከተማ ያዘጋጀው ስልጠና ተጠናቀቀ።

  በገቢ ግብር አዋጁ ዙሪያ ለጋዜጠኞች ስልጠና መስጠት ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት በክልላችን ፍትሃዊ፣ ዘመናዊና ቀልጣፋ የታክስ አስተዳደር ስርዓት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የብዙሃን መገናኛ ተቋማት ተሳታፊ እንዲሆኑና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ፍትሃዊ የህዝብ ተደራሽነት ስራ መስራት የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነው። ስልጠናው በባለስልጣኑ ከፍተኛ ባለሙያዎች ተዘጋጅቶ የተሰጠ ሲሆን በገቢ ግብር አዋጁ ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ የቀረበበት ነበር።

  ባለስልጣኑ መሰል ስልጠናዎችን ለአጋርና ባለድርሻ አካላት እንዲህ በተደራጀ ሁኔታ የስልጠና ሰነድ በማዘጋጀት ለየት ባለ ሁኔታ ሲሰጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ቢሆንም ለፍትህ አካላት፣ ዳኞችና አቃቤ ሕጎች በገቢ ግብር አዋጁ አተገባበር በ2005 ዓ.ም የአንድ ቀን ስልጠና መሰጠቱ የሚታወስ ነው።
  በስልጠና የተሳተፉ በቁጥር 70 የሚሆኑ ሰልጣኞች ስልጠናው የዘገየ ቢሆንም አስፈላጊ መሆኑን፣ ለስራቸው አጋዥ እንደሚሆንላቸውና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ዘገባ ለመስራት እንደሚያስችላቸው ገልጠዋል። ከግብር ጽንሰ-ሀሳብና አተገባበር አኳያ ባለስልጣኑ ተከታታይ የእውቀትና ክህሎት ግንባታ መስጠት የሚያስፈልገው በመሆኑ የራሱ የሆነ የቴሌቪዥን፣ የሬዲዮና የጋዜጣ የአየር ሰዓትና ዓምድ ሊኖረው ይገባል፡፡ ለዚህም ከሚመለከታቸው አመራሮች ጋር በመምከር ነጻ የአየር ሰዓት እንዲኖረው ማድረግ ተገቢ መሆኑንም ጠቁመዋል።

  ከህብረተሰቡና ከራሳቸው የታዘቧቸውን አስተያየትና ጥያቄዎች ከባለስልጣኑ፣ ከህብረተሰቡና ከብዙሀን መገናኛ ተቋማት ምን ይጠበቃል? እንዴትስ በጋራ መስራት ይቻላል? ባለስልጣን መ/ቤቱንና ግብር ከፋዮችን እንዴት ማቀራረብና ፍትሃዊ የግብር አስተዳደር ስርዓት ማስፈን ይቻላል የሚሉ ጉዳዮችን በማንሳት በሰፊው የተወያዩ ሲሆን ላነሷቸው ጥያቄዎችም ተገቢውን ምላሽ አግኝተዋል።
  በስልጠናው ማጠናቀቅያ ዕለት የተገኙት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስማማው ማሩ ከብዙሀን መገናኛ ተቋማት ጋር የምናደርገውን ተመሳሳይ ስልጠና በማስፋት በቀጣይ ለሌሎችም የብዙሀን መገናኛ ተቋማትና ጋዜጠኞች ተከታታይ የስልጠና መድረኮች እንደሚዘጋጁ እና የብዙሀን መገናኛ ተቋማትም ባለስልጣኑ በሚያደርጋቸው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች እስካሁን ያልተለዩን ቢሆንም በቀጣይ ከዚህ በተሻለ ሁኔታ ልማታዊ ጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር በመላበስ የባለስልጣኑን ዓላማ፣ ስልጣንና ተግባር በመረዳት አሰራራችንን ቀልጣፋና ፍትሃዊ ለማድረግ በምናደርገው ጥረት እንዳትለዩን በማለት በራሳቸውና በባለስልጣኑ ስም መልዕክት አስተላልፈዋል።