Web Content Display Web Content Display

Return to Full Page

የባለስልጣኑ ሰራተኞች 23 ኛውን የግንቦት 20 በዓል በደማቅ ሁኔታ አከበሩ

    የአማራ ገቢዎች ባለስልጣን ሰራተኞች የግንቦት 20ን 23ኛ በዓል ከዋዜማው ጀምረው እስከ ግንቦት 23 2006 ዓመተ ምህረት ድረሰ በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ አከበሩ።


    "ሩቅ አስባ ሩቅ ለማደር እየተጋች ያለች ሀገር" በሚል መሪ ቃል የተከበረው በዓል ዘንድሮ በተለየ ሁኔታ የግንቦት 20 ፍሬዎችን በሚያሳይ በደማቅ ሥነ-ስርዓት ነው። በዕዝ ኢኮኖሚ ተጠፍንጎ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ አላሰራ ብሎ የነበረው የደርግ መንግስት ድል ከተመታበት ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓመተ ምህረት በኋላ መላው ህዝብ እንደ አቅሙና ፍላጎቱ ያለውን ሃብት አሟጦ መስራት የሚያስችል ሁኔታ ስለተፈጠረለት አያሌ ባለሀብቶች ተፈጥረው ቢሊየነር መሆን ችለዋል። በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች በመፈጠራቸውም በአገራችን ዘርፈ ብዙ የስራ መስኮች ተፈጥረዋል። በርካታ በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ወጣቶች የኢንደስትሪ ሽግግር አካሂደዋል። በርካታ አርብቶ አደሮች ወደ አርሶ አደርነት ተሸጋግረው በጓሯቸው እሸት መቅመስ ችለዋል። እነዚህ እና ሌሎች የስራ አማራጮች በመበራከታቸው የአገሪቱ የውስጥ ገቢ እያደገ እና እያደገ ይገኛል።


    አገራችን ከብድርና ከእርዳታ ተላቃ በራሷ ገቢ መተዳደር የምትችለው በርካታ ስራ ፈጣሪ ቢሊየነሮች ሲበራከቱ በመሆኑ በዚህ ዘርፍ ለሚሰማሩ ልማታዊ ስራ ፈጣሪዎች የአገር ውስጥና የውጭ አገር የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ፍትሃዊ የቀረጥ አጣጣል ዘዴ በመጠቀም የገቢና ወጭ ምርቶችን ለማጣጣም ጥረት እየተደረገ ይገኛል።


    የባለስልጣኑ ሰራተኞች የዘንድሮውን በዓል ያከበሩት በተለያየ ሁኔታ ሲሆን የመጀመሪያው በሙሉአለም የባህል ማዕከል ከተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት የተውጣጡ የመንግስት ሠራተኞች ጋር በፓናል ውይይት በመሳተፍ ነው። ውይይቱ በቅድመ እና ድህረ 1983 የነበሩና ያሉ እውነታዎች የተዘከሩበት በርካታ አስተያየትና ጥያቄዎች የተስተናገዱበት እና የጋራ መግባባት የተፈጠረበት መድረክ ነበር። በመቀጠል በዕለቱ ግንቦት 20 ቀን 2006 ዓመተ ምህረት ከባለስልጣኑ መስሪያ ቤት በመነሳት ባህር ዳር ሁለገብ ስታዲየም ድረስ ስርዓት በተሞላበት ሁኔታ መሪ ቃሎችን በማስተጋባት፣ ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብና ቀስቃሽ መዝሙሮችን በማሰማት በሰላማዊ ሰልፍ ተከብሯል።


    በመጨረሻም ከግንቦት 20 ፍሬዎች መካከል የጣና ፍሎራ አበባ ማምረቻ ኢንቨስትመንት ግንቦት 23 ቀን 2006 ዓመተ ምህረት የተደረገው ጉብኝት ልማትና ዕድገቱን በተግባር ማረጋገጥ የተቻለበት ነበር። የጣና ፍሎራ አበባ ማምረቻን በአካል እንዳየነው የአበባ ምርት እንዲህ በብዙ ዘመናዊ መሳሪያዎች ታግዞ ለውጤት እንደሚበቃ በዓይኑ ላላየ ቢነግሩት አያምንም። ይሀ የኢንቨስትመንት ዘርፍ በክልላችን ፈር ቀዳጅ የአበባ ማምረቻ ከመሆኑ በተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ብዙ ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞችን ቀጥሮ የስራ ዕድል እንዲያገኙ ያደረገ ለባህር ዳር ከተማና አካባቢው ወጣቶች ባለውለታ ነው። ከግንቦት 20 ፍሬዎች ከተለያዩ የገቢ ዘርፎች የሚሰበስበው ገቢ ከዓመት ዓመት እድገት እያሳየ የሚገኝ በመሆኑ በቀጣይም በድህነት ላይ የሚደረገውን ዘመቻ በማስፋት በክልላችን የእርሻና ኢንዱስትሪ አማራጮችን በማጠናከር ከግብር እና ታክስ በሚሰበሰበው ገቢ አስተማማኝ የእድገት መሠረት መጣል እንደሚቻል አንዳንድ የጉብኝቱ ተሳታፊዎች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።