Web Content Display Web Content Display

 

ስልጠና ተሰጠ

በአብክመ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ኮሚሽን የተለያዩ ሲስተሞች ላይ ለባለሙያዎች ስልጠና ሰጠ፡፡ በኮሚሽኑ አዘጋጅነት ከመስከረም 20 እስከ 23/2012 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ በተሰጠው ስልጠና የዞንና የክልል ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል፡፡

ከመስከረም 20 እስከ 21/2012 ዓ.ም ድረስ በተሠጠው ስልጠና ከሁሉም ዞኖች የተውጣጡ የኢኮቴ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን ስልጠናው ያተኮረው ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል ለሚደረገው የሪፖርት ልውውጥ የሚያገለግል sticc info የተሰኘ ዌብ ቤዝድ አፕሊኬሽን ሲስተም ነው፡፡ ሲስተሙ የተለማው በኮሚሽኑ ባለሙያዎች መሆኑ በስልጠናው ወቅት ተመለክቷል፡፡

በተመሳሳይ ከመስከረም 22 እስከ 23/2012 ዓ.ም የተሰጠው ስልጠና በፖርታል አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ሲሆን የፖርታሉ ተጠቃሚ የክልል ተቋማት የህዝብ ግንኙነትና የኢኮቴ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡ ፖርታሉ ሃያ ስድስት የክልል ተቋማትን ያካተተ ሲሆን መገኛ አድራሻውም www.amhara.gov.et ነው፡፡ ፖርታሉ ውስጥ የተካተቱ ተቋማት የየተቋማቸውን መረጃዎች በየጊዜው በማስገባት ለህብረተሰቡ ማድረስ እንደሚገባ በስልጠናው ወቅት ተጠቁሟል፡፡

 

ኮሚሽኑ የእቅድ አፈፃፀሙን ገመገመ ፡፡

የአብክመ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ኮሚሽን የ2011 በጀት አመት የእቅድ አፈፃፀም ግምገማና የ2012 ዓ.ም እቅድ ትውውቅ አደረገ፡፡ በእንጅባራ ከተማ ነሐሴ 09/2011 ዓ.ም ከዞን አስተዳዳሪዎች፣ አስተዳደር ጽ/ቤት ሃላፊዎች፣ ኢኮቴ አስተባባሪዎች፣ ከምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ፣ ከህዝብ ክንፍና አጋር አካላት እንዲሁም ከኮሚሽኑ ሰራተኞች ጋር ባካሄደው መድረክ የ2011 በጀት አመት የእቅድ አፈፃፀሙን በመገምገም የ2012 ዓ.ም እቅዱን አስተዋውቋል፡፡

በዕቅድ አፈጻጸም ግምገማው እንደተገለጸው በአመቱ 360 ለሚሆኑ የትምህርት ባለሙያዎች፤ መምህራንና ተማሪዎች በሳይንስና ፈጠራ ክበባት ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ የተፈጠረ ሲሆን 589 ትምህርት ቤቶች በተደራጀ ሁኔታ የሳይንስና ፈጠራ ክበባት እንዳቋቋሙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

አገልግሎት በመስጠት ላይ በሚገኙ  የማህበረሰብ ሁለገብ መረጃ ማዕከላት በአጠቃላይ ለ89 ወጣቶች የስራ እድል የተፈጠረላቸዉ ማዕከላቱ 410,368.00 (አራት መቶ አስር ሽህ ሶስት መቶ ስልሳ ስምንት) ብር ካፒታል እንዳላቸዉ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በሪፖርቱ እንደተገለጸው በበጀት ዓመቱ 108 ድረ-ገጾችን ለማልማት ታቅዶ 78 ድረገጽ የተለማ ሲሆን አፈፃፀሙም 72.22% መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ከአግሮ ቢግ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከአማራ ብረታ ብረት፣ ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ ጋር ዉል በመያዝ ሶስት የሩዝና የሥንዴ ማጨጃ ማሽኖችንና አንድ የበቆሎ መሰብሰቢያ ማሽን በድምሩ 4 የሰብል ድህረ ምርት ቴክኖሎጅዎችን ከውጭ በማስገባት ቴክኖሎጂዎችን ለማሸጋገር የሙከራ ስራ እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡በኮሚሽኑ የአፈጻጸም ሪፖርት እንደተገለጸው በባህር ዳር አይ.ሲ.ቲ ቢዝነስ ኢንኩቤሽን ማዕከል 6 አዳዲስ ካምፓኒዎችን በኔትወርክና ሶፍት ዌር ልማት እንዲሁም በጥገና ሙያዎች መቀበል ተችሏል፡፡ በበጀት አመቱ ለ1839 ተጠቃሚዎች የቪዲዮ ኮንፈረንስ አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን ይህን አገልግሎት መጠቀም በመቻሉ ብር 9,327,028.00 (ዘጠኝ ሚሊዮን ሶስት መቶ ሀያ ሰባት ሽህ ሀያ ስምንት) የሚገመት ወጪ ማዳን ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ከአይ.ሲ.ቲ ዕቃዎች ጥገናና የማስተካከል ሥራ ከመንግሥት ሊወጣ የነበረን ብር 5,913,857.33 ወጪ ማዳን መቻሉ በሪፖርቱ ተገልጧል፡፡

 

በሪፖርቱ በበጀት አመቱ የተመዘገቡ መልካም ውጤቶች፣ በሥራ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ተለይተው ቀርበዋል፡፡ተወያዮቹ ከእቅድ አፈጻጸም ግገማው በተጨማሪ በኮሚሽኑ የተለማው STICC Info Reporting System ተዋውቋል፣ በተጨማሪም በኮሚሽኑ የ2012 በጀት አመት እቅድ ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡በመጨረሻም በበጀት አመቱ የተሻለ አፈጻጸም በማስመዝገብ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ የወጡ ዞኖች የዋንጫና የሰርቲፊኬት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፤ በዚህም መሰረት 1ኛ ሰሜን ሸዋ፣ 2ኛ ደቡብ ወሎ እንዲሁም 3ኛ ማዕከላዊ ጎንደር ዞን በመውጣት ሽልማታቸውን ተረክበዋል፡፡በውይይት መድረኩ ከየዞኑ ዋና አስተዳዳሪዎች፣ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የኢኮቴ አስተባባሪዎች፣ ከርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት፣ ከክልል ምክር ቤት የሰው ሃብትና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ከህዝብ ክንፍ ተቋማት፣ ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ከፖስታ አገልግሎት ድርጅት እና የኮሚሽኑ ሰራተኞች ተሳትፈዋል፡፡