Web Content Display Web Content Display

የውጭ ቴክኖሎጅዎችን ወደ ክልሉ ለማስገባት፣ ለማላመድና ለመጠቀም እንዲሁም የክልሉን ኢንዱስትሪያዊ ዕድገት በሳይንሳዊ ምርምሮች ለመደገፍ የሚያስችል ሆኖ በሀገር ደረጃ የተቀረፀውን ብሄራዊ የሣይንስ፣ የቴክኖሎጅና የኢኖቬሽን ፖሊሲ በክልሉ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዝ አቅም መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤

በክልሉ ውስጥ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጅን በማልማትና በማስፋፋት ሴክተሮች፣ ሕዝብና መንግስት በቂ፣ ወቅታዊና ጥራት ያለው መረጃ በማግኘት የአገልግሎት አሰጣጣቸውን በጥራትና በፍጥነት ማቅረብ እንዲችሉ አግባብ ካላቸው የፌደራል መንግስት አካላት ጋር የጋራ ቅንጅታዊ አሠራርን በማስፈን አስተማማኝ የሆነ የኢንፎርሜሽንና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጅ መሠረተልማት በመዘርጋት ለክልሉ ሁለንተናዊ ልማት መፋጠንና ለመልካም አስተዳደር መጐልበት በዕውቀትና መረጃ ላይ የተመሠረተ አንድ ወጥ ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ ይኸው ዘርፍ እንደ አንድ ክፍለ ኢኮኖሚ ተለይቶ መልማት በሚገባው ደረጃ እንዲበለፅግና በክልሉ ልማት ረገድ በዘርፉ የተሠማራው የግል ሴክተር የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና በዚሁ ዙሪያ የሚገኘውን ዕውቀትና መረጃ አይነተኛ የዕድገት መሳሪያ አድርጐ መጠቀም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ የክልሉ ህብረተሰብ ከዓለም አቀፍ ዕውቀትና ከየዕለቱ የመረጃ ፍሰት ተጠቃሚ የሚሆንበትን ዕድል በመፍጠርና በሃገራዊ ጉዳዮች ውሣኔ አሰጣጥ ተሣታፊ በማድረግ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደሩን ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችልና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ በቂ የሙያ ዕውቀትና ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ማፍራት በማስፈለጉ፤

የክልሉ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጅ ልማት በተቀናጀ ሁኔታ በሥራ ላይ ውሎ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመዘገብ ዘርፉን ወጥነት ባለው መንገድ የሚያስተባብር፣ የሚደግፍ፣ አፈፃፀሙን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማከናወን የሲስተም ቀረፃና የአገልግሎት ስታንዳርድ በማዘጋጀት ሁሉንም ተግባራትና እንቅስቃሴዎች በቅርብ የሚከታተልና ጥራቱን የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ አካል ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ የአማራ ክልል ምክር ቤት በተሻሻለው የብሄራዊ ክልሉ ህገ-መንግስት አንቀፅ /49/ ንዑስ አንቀጽ 3/1/ ድንጋጌ ስር በተሰጠው ስልጣን መሠረት ይህንን አዋጅ አውጥቷል